በትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር አለሙ ስሜ የተመራ ልዑክ በጅቡቲ የስራ ጉብኝት እያደረገ ነው፡፡ዶክተር አለሙ ስሜ በጅቡቲ ቆይታቸው ከሀገሪቱ መሠረተልማት ሚኒስትር ሀሰን ኢብራሂም ጋር ተወያይተዋል።
ዶክተር አለሙ÷ ኢትዮጵያ ከጅቡቲ ጋር ያላትን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት አጠናክሮ ለማስቀጠል ከምን ጊዜውም በላይ ዝግጁ መሆኗን ተናግረዋል። የኢትዮጵያ እና የጅቡቲ ታሪካዊ ግንኙነት በኢኮኖሚና ማህበራዊ ጉዳዮች ጠንካራና ለቀጠናው ምሳሌ እንደሆነም አንስተዋል፡፡
ለቀጠናው ምሳሌ የሆነው የኢትዮጵያ እና የጅቡቲ ታሪካዊ ግንኙነት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል። የሁለቱ ሀገር ህዝብ ድንበር ፣ ቋንቋ ፣ ሐይማኖት እና ባህል ይጋራል ያሉት ሚኒስትሩ÷ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በሌላ መልኩ ጅቡቲ የኢትዮጵያ ገቢ እና ወጪ ንግድ ማሳለጫ መንገድ እንደመሆኗ መጠን በዚህ መንገድ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በጋራ መፍታት እንደሚገባ ጠቁመዋል።
ሀሰን ኢብራሂም በበኩላቸው÷ ጅቡቲ ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ግንኙነት በጽኑ መሠረት ላይ የተመሠረተ ስለሆነ በመሰረተ ልማትም ሆነ በሌሎች የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን በሚያጠናክሩ መስኮች አብሮ ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡