127ኛውን የዓድዋ ድል በዓል በኤምባሲው ቅጥር ግቢ የጅቡቲ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ክቡር ማህሙድ አሊ ዩሱፍ ፣ የጅቡቲ ንግድና ቱሪዝም ሚኒስትር ክቡር መሃመድ ዋርሳማ ዲሬ፣ በጅቡቲ የአምባሳደሮች ዲን ክቡር አብደላ ሙሳለም እና የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች፣ ዲፕሎማቶች፣ ኢትዮጵያውያንና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ተከብሯል፡፡

በበዓሉ መክፈቻ ላይ ክቡር አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ ንግግር ያደረጉ ሲሆን ኢትዮጵያውያን ለሀገራቸው ህልውና እና ነጻነታቸው መከበር በዓድዋ ዘመቻ ያሳዩት ተጋድሎ በጦር ሜዳ ውሏቸው በሰሩት ጀብድ ብቻ የታጠረ አልነበረም ብለዋል፡፡

ድሉ የጣሊያንን እና ሌላውንም የአውሮፓ ሕዝብ ያስገረመው የጦር ምርኮኞች አያያዝም ጭምር ነበር ነው ያሉት።

የዓድዋ ድልን ሁሌም የምናከብረው በዘመኑ የተገኘውን ድል ለመዘከርና በታሪክ ሁነትነቱ ብቻ ሳይሆን ላለንበትና ለመጪ ዘመናት ባለው ፋይዳ ትምህርት ለመቅሰምም ጭምር ነው ሲሉም ገልጸዋል።

በታሪክ አጋጣሚ ኢትዮጵያ በጅቡቲ ቆንስላ ጽ/ቤቷን የከፈተችው ከአድዋ ድል ማግስት ነው። የሁለቱ አገራት ግንኙነት በታሪክ፣ በደምና በድል የተሳሰረ ከመሆኑም በላይ የመጪው ዘመን ኢኮኖሚያዊና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከፍታን ይበልጥ ማጠናከር እንዳለብን  አመላካች  ነው በማለት ንግግራቸውን አጠናቅቀዋል።

በንግግራቸው ከአድዋ ድል ሁለት የተማርናቸው ዋና ዋና ትምህርቶች አሉን ያሉት ደግሞ የጅቡቲው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ክቡር ማህሙድ አሊ ዩሱፍ ሲሆኑ አንደኛው የአገርን ነጻነት እና ሉዓላዊነት ለማስከበር ይህ ነው ተብሎ ዋጋ የማይወጣለትን መስዋዕትነት መክፈል የግድ መሆኑንና እና ሁለተኛው ደግሞ የአመራር ቁርጠኝነት ባለበት ሁኔታ የሕዝቡ ጠንካራ ወኔ ታክሎበት ተራሮችን ማንቀሳቀስ የሚችል አቅም መፍጠር እንደሚቻል ያየንበት ነው ብለዋል የአድዋ ድልን።

በመቀጠል በክቡራን እንግዶች የዳቦ ቆረሳ ፕሮግራም የተካሄደ ሲሆን የሀገራችን የቡና አፈላል ስነ ሥረዓትም ተከናውኗል። 

በመጨረሻም በታዋቂው ድምጻዊ አቡ የዚድ የታጀበ የመድረክ ዝግጅት የቀረበ ሲሆን በተጋባዥ ተወዛዋዦች የሀገራችንን የባህላዊ ውዝዋዜዎችና ጭፈራዎች ለታዳሚዎች በማሳየት ፕሮግራሙ ተጠናቋል።

Loading

Disclaimer: The official text of the Embassy Website is the English language version. Any discrepancies or differences created in translations are not binding and have no legal effect for compliance or enforcement purposes.

X