ክቡር አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ በጅቡቲ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን እና ትውለደ-ኢትዮጵያዊያን ጋር በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አደረጉ
በጅቡቲ የኢ.ፌ.ዲ. ሪ ኤምባሲ ልዩ መልዕክተኛ እና ባለሙሉ ስልጣን ክቡር አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ ነዋሪነታቸውን በጅቡቲ ካደረጉ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ጋር ዛሬ የካቲት 17 ቀን 2015 ዓ.ም ውይይት አድርገዋል።
በውይይቱ ላይ የኃይማኖት አባቶች፣ አገር ሽማግሌዎች፣ የተለያዩ ከልማትና ከሴቶች ማህበራት አደረጃጀቶች የተውጣጡ የዳያስፖራ አባላት እና በነጻ የንግድ ቀጠና እየሰሩ ከሚገኙ ኢትዮጵያውያንንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ተሳትፈውበታል።
በውይይቱ ላይ ክቡር አምባሳደሩን ጨምሮ በሚሲዮኑ ምክትል አምባሳደር እና ከፍተኛ ዲፕሎማቶች በቅርቡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አባቶች መካከል በነበረው አለመግባባት ዙሪያ፣ የሰላም ስምምነቱን በተመለከተ እና በሌሎች የሀገራችን ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ እንዲሁም በጅቡቲ ስለሚገነባው የኢትዮጵያ ኮሚዩኒቲ ትምህርት ቤት፣ በሚሲዮኑ አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ እና በተለያዩ የልማት ስራዎች ዳያስፖራው ከሚሲዮኑ ጋር ይበልጥ ተቀራርቦ መስራት በሚቻልባቸው ጉዳዮችን በተመለከተ ማብሪሪያ ሰጥተውበታል።
የተደረገውን ገለፃ መነሻ በማድረግም የመድረኩ ተሳታፊዎች በወቅታዊ የሀገራችን ጉዳዮች፣ በፓስፖርት እድሳት የዋጋ ጭማሪ እና የኮሚኒቲ ትምህርት ቤቱን በተመለከተ ላነሷቸው ጥያቄዎች ክቡር አምባሳደር ብርሃኑ ምላሽ ሰጠተዋል።
ክቡር አምባሳደሩ በተጨማሪም በሰጡት ማብራሪያ የዳያስፖራ አባላት አንድነታቸውን በማጠናከር በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መረጃዎችን ከትክክለኛ ምንጭ በመውሰድ ለሌሎች በማስተላለፍና ለሀገራችን ሰላም እና መረጋጋት የሚቻለውን ድጋፍ በማድረግ የበኩላቸውን ሀገራዊ ግዴታ እንዲወጡ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
የመድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው በቀጣይ ኤምባሲው የሚሰጣቸው የመረጃ ግብዓቶችን በመጠቀም ከኤምባሲው ጋር በጋራ በሀገራዊ ልማት ላይ እንደሚሰሩ ገልፀዋል። በተጨማሪም የመድረኩ ተሳታፊዎች በጅቡቲ ለሚገነባው የኮሚኒቲ ትምህርት ቤት ግንባታ የሚውል ሀብት ለማሰባሰብ እና እራሳቸውም ያላቸውን በማዋጣት ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ ቃል ገብተዋል።