በጅቡቲ የአማራ ልማት ማህበር ጅቡቲ ቅርንጫፍ ዛሬ ግንቦት 25 ቀን 2015 ዓ.ም በኢትዮጵያ ኮሚዩኒቲ ማህበር አደራሽ ጠቅላላ ጉባዔውን በማካሄድ አዳዲስ የስራ አስፈጻሚ አባላት ምርጫ አካሂዷል፡፡
ጉባዔውን በጅቡቲ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ኤምባሲ ልዩ መልዕክተኛ እና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉ ሲሆን፤ በንግግራቸውም ለአንድ አገር ዕድገት ዜጎች የሚያደርጉት አስዋጽኦ ከፍተኛ ድርሻ መሆኑን፤ ዕድገት በልማት እንደሚሳካ፣ ልማት ደግሞ በትብብር መሰራት እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡
ለዚህም የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግስት ዘላቂና አስተማማኝ ሰላም በማስፈን ዋነኛ ጠላታችን የሆነውን ድህነትን ለማሸነፍ እና የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ፖሊሲና ስትራቴጂ ቀርጾ በአገር ውስጥና ከአገር ውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን በማሰለፍ ፈጣንና ተከታታይ እድገት ለማስመዝገብ በተደረገው እንቅስቃሴ ባለፉት ጊዚያት ጥሩ ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል፡፡
ለኢኮኖሚ እድገት መመዝገብ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልድ ኢትዮጵያዊያን ያላቸው ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን አስገንዝበው ወደፊትም አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አሳስበዋል።
የአማራ ልማት ማህበር የተቋቋመበት ዓላማ እንደ አንድ ህዝባዊ የልማት ማህበር ክልሉ እንዲለማ በሚደረገው ጥረት ውስጥ ከህዝቡ፣ ከግብረ-ሰናይ ድርጅቶችና ከተለያዩ ምንጮች ሀብት በማሰባሰብ በመንግስትና በሌሎች የልማት ኃይሎች ሊሟሉ ያልቻሉ ክፍተቶችን ለመሙላት መሆኑን ገልፀው፤ በጅቡቲ የአማራ ልማት ማህበር ጅቡቲ ቅርንጫፍ በክልሉ ልማት ላይ እያበረከተ ያለውን አስተዋጾ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።
የማህበሩ ጠቅላላ ጉባኤ የተከናዎኑ ስራዎችንና የማህበሩን የኦዲት ሪፖርት በማዳመጥና በመወያየት አጽድቋል። እንዲሁም ለቀጣይ የልማት ማህበሩ መሻሻልና ከፍ ያለ ደረጃ ላይ ለማድረስ እንዲቻል በሌሎች የልማት ስራዎች ላይ የተሳካ ልምድ ያላቸው፤ በተሰማሩበት የስራ መስክ ውጤት ያስመዘገቡና በማህበረሰቡ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸውን አመራሮች ጉባኤው መርጧል።
የተመረጡ ስራ አስፈጻሚ አባላት የስራ ክፍፍል በማድረግ ኃላፊነታቸውን ተረክበው በቀጣይ ማህበሩን በማጠናከር የሚመሩ ይሆናል።