በጅቡቲ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ኤምባሲ በጅቡቲ ከሚገኘው የዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት ቢሮ ጋር በመተባባር 86 ፍልሰተኞች በባቡር ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ አደረገ፡፡
ከፍልሰተኞች መካከል 30 ያህሉ በየመን በአስከፊ ችግር ውስጥ ቆይተው ወደ ጅቡቲ የገቡ ሲሆኑ ቀሪዎቹ ደግሞ ወደ መካከለኛው ምስራቅ ለመሻገር ጅቡቲ ከገቡ በኋላ ባህር የመሻገር ሀሳባቸውን ለመቀየር የተገደዱ ናቸው፡፡
በህገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች በመካከኛው ምስራቅ አገራት በአጭር ጊዜ ለመክበር በሚል የቀቢጸ ተስፋ ምኞት ተታልለውና ከፍተኛ ገንዘብ ከፍለው ከሀገራቸው የወጡት ፍልሰተኞቹ በመሸጋገሪያና መዳረሻ ሀገራት ለረሃብ፣ ለውሃ ጥም፣ ለጤና መታወክ፣ ለከፍተኛ እንግልትና ተያያዥ ችግሮች የተዳረጉ ናቸው፡፡
ከኢትዮጵያ- ጅቡቲ- የመን የሚደረገው ህገ-ወጥ የሰዎች ፍልሰት በሞትና ልዩ ልዩ አደጋዎች የተሞላ በመሆኑ፣ ኤምባሲው የአገራችን ወጣቶች በህገ-ወጥ ደላሎች የውሸት ስብከት በመታለል ውድ ህይወታቸውን አደጋ ላይ ጥለው በዚህ አደገኛ የጉዞ መስመር ከመንቀሳቀስ እንዲቆጠቡ መልዕክቱን ያስተላልፋል።