የጅቡቲ የባህር ዳርቻ ጥበቃ ሀይል በጅቡቲ በኦቦክ ክልላዊ መስተዳደር ጋህሬ የባህር ዳርቻ አካባቢ 253 ኢትዮጵያዊያን ፍልሰተኞችን ጭና ወደ የመን የምትጓዝ ህገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪ ጀልባ በቁጥጥር ስር በማዋል ፍልሰተኞቹን ከሞት አደጋ ታድጓል ፡፡
ከፍልሰተኞቹ መካከል 98ቱ ሴቶች ናቸው፡፡
የጅቡቲ የባህር ጠረፍ ጥበቃ እንዳስታወቀው ጀልባዋ በቁጥጥር ስር ባትውል ኖሮ ከአቅም በላይ በመጫኗ የመስጠሟና የፍልሰተኞች ህይወት የማለፉ እድል ከፍተኛ ነበር ፡፡
ለፍልሰተኞቹ አስፈላጊው ድጋፍ ተደርጎላቸው ወደ ሀገራቸው እንዲገቡ ተደርጓል፡፡
ኃይሉ የአሁንን ከስተት ጨምሮ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ ህገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪ ጀልባዎችን በቁጥጥር ስር በማዋል ከ1000 በላይ ኢትዮጵያዊያን ህይወት መታደግ ችሏል፡፡
አራት የውጭ ዜጎች በህገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪነት ተጠርጥረው ለፍርድ መቅረባቸውንም ማረጋገጥ ተችሏል፡፡
ኢትዮጵያውያን ፍልሰተኞቹ ህገወጥ ጀልባዎችን በመጠቀም ከየመን ወደ ጅቡቲ እንዲሁም ከጅቡቲ ወደ የመን በሚያደርጉበት ጉዞ በጅቡቲ የባህር ዳርቻዎች ተደጋጋሚ የጀልባ መገልበጥ አደጋዎች፣ በመንገድ ላይ የመኪና አደጋዎች፣ በውሀ ጥምና በወባ ምክንያት በርካታ ዜጎቻችን ለሞት እየተዳረጉ ስለሚገኙ ፣ ኤምባሲው ዜጎቻችን በህገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ተታለው ይህን አደገኛ የጉዞ መስመር እንዳይከተሉ ያሳስባል፡፡
ኤምባሲው የጅቡቲ የባህር ዳርቻ ጥበቃ ሀይል ፍልሰተኛ ዜጎቻችንን ለመታደግ ለሚያደርጓቸው ዘመቻዎች ምስጋናውን ለመግለፅ ይወዳል፡፡