በጅቡቲ ከተማ ከንቲባ ክቡር አቶ ሰኢድ ዳውድ ሙሀመድ የተመራ የልኡካን ቡድን በሁለቱ እህትማማች ከተሞች መካከል ያለውን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ትስስር ለማጠናከር የሶስት ቀናት የስራ ጉብኝት አድርጓል።
የድሬዳዋ ከተማ ከንቲባ ክቡር አቶ ከድር ጁሀር ለጅቡቲው አቻቸው በጽህፈት ቤታቸው ደማቅ አቀባበል አድርገውላቸዋል። ጉብኝቱ በአጠቃላይ በያዝነው ዓመት መስከረም ወር ላይ የሁለቱ ከተማ ከንቲባዎች በጅቡቲ የተፈራረሙትን የመግባቢያ ሰነድ ተግባራዊ ለማድረግ የተደረገ ሲሆን የከተሞቹ ንግድ እና ኢንቨስትመንት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል።
በከንቲባ መሀመድ የተመራ የጅቡቲ የቢዝነስ ልዑካን ቡድን የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣና ውስጥ የሚገኙትን የመኪና መገጣጠሚያ እና የጅቡቲ አሬይ ሲሚንቶ ፋብሪካ የማሸጊያ ምርትን ጨምሮ ጎብኝቷል። የልዑካን ቡድኑ በጅቡቲ አቅራቢያ ያለውን የድሬዳዋን ነጻ ንግድ ቀጠና እና ኢንዱስትሪ ዞን ተጠቅሞ በሁለቱ ከተሞች መካከል ያለውን ጠንካራ ግንኙነት እና ኢኮኖሚያዊ ትስስር የሚያጠናክር መልካም አጋጣሚ አድርጎታል። የልዑካን ቡድኑ የከተማውን ፖሊስ ኮሚሽን፣ ናሽናል ሲሚንቶ፣ ስታዲዮም፣ የሲቪክና ስፖርት ማዕከሎች እንዲሁም የቀድሞውንና አዲሱን የባቡር ጣቢያዎችም ጎብኝቷል።
የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ በጎረቤት አገራት ተደራሽ ለማድረግ በጅቡቲ ሶስት ዙር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብሮች መደረጋቸው እና ከሩብ ሚሊዮን በላይ ችግኞች ወደ ጅቡቲ መላኩን በማስታወስ፣ የልኡካን ቡድኑ በድሬዳዋ የችግኝ ጣቢያን ጎብኝቷል።
ከተሞቹ የመግባቢያ ሰነዱን ተግባራዊነት የሚቆጣጠሩ ስድስት ከሁለቱ ከተሞች የተውጣጡ ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎችን በመምረጥ ቴክኒካል ኮሚቴ አቋቁሟል። የቴክኒካል ኮሚቴው የጋራ ስብሰባዎችን የማዘጋጀት ፣የሂደት ክትትል እና ትግበራ ሪፖርት የማዘጋጀት ሀላፊነት ያለበት ሲሆን በአመት አንድ ግዜ በመገናኘት እንቅስቃሴዎችን ለመገምገም የሚያስችል ስምምነት ተፈራርሟል።
ጉብኝቱ በጅቡቲ እና ኢትዮጵያ መካከል ያለውን ጠንካራ ትስስር የሚያጎላ ሲሆን፥ ሁለቱም ከንቲባዎች በሁለቱ እህትማማች ከተሞች መካከል ያለውን ትብብር እና የጋራ መግባባት ለማስቀጠል በትብብር ለመስራት ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል።